1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

ተከሳሽ የምክር ቤት አባላት ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ

ዓርብ፣ መጋቢት 27 2016

ተከሳሾቹ ከሳምንት በፊት እሥር ቤት ውስጥ ሆነው በፃፉት ደብዳቤ "ማንነትን መሠረት ያደረገ ስድብ፣ ዘለፋ ፣ ማስፈራራት፣ ዛቻ ፣ ድብደባ እና ዝርፊያ" እንደተፈፀመባቸው ገልፀው ነበር። በዛሬው ችሎት ላይም አቶ ክርስትያን ታደለ ደረሰብኝ ያሉትን የመብት ጥሰት ለፍርድ ቤቱ መግለጻቸውን ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ በስልክ ነግረውናል።

https://p.dw.com/p/4eTTG
የዛሬዉ ችሎት የተሰየመዉ የተከሳሾችን እምነት ክሕደት ለመስማት ነበር (ፎቶ ከክምችታችን)
ዛሬ ፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተከሳሾች በአሸባሪነት ከተከሰሱት 52 ተጠርጣሪዎች 14ቱ ናቸዉ (ፎቶ ከክምችታችን)ምስል Seyoum Hailu/DW

ተከሳሽ የምክር ቤት አባላት ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ

የኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት  ካሰራቸዉና ከከሰሳቸዉ 52 ተጠርጣሪዎች መካከል14ቱ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ በፌዳራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።ፍርድ ቤት ከቀረቡት ተከሳሾች  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ክርስቲያን ታደለና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል  ዮሐንስ ቧያለዉ ይገኙባቸዋል።ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት የቀረቡት የእምነት ክሕደት ቃላቸዉን ለመስጠት ነበር።ይሁንና ተከሳሾቹ በደል ደርሶብናል በማለታቸዉ ችሎቱ ተከሳሾች ያቀረቡትን አቤቱታ ሲያደምጥ ዉሏል። 

ጋዜጠኞች "ለችሎት የዘገባ ፈቃድ አላቀረባችሁም" በሚል ዘገባ የተከለከሉበት የዛሬው ችሎት

ከ52 ቱ ተከሰሾች 14ቱ በተገኙበት፣ ሰባት የተከሳሽ ጠበቆች በታደሙበት ዛሬ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሕ ችሎት አዳራሽ በዋለው የፍርድ ሂደት ለተከሳሾች የክስ ዝርዝር ሊነበብ ነበር ቀጠሮ የተያዘው።

ይሁንና ከተከሳሽ ጠበቆች  የክስ ንባቡ "ሥነ ሥርዓታዊ" ቢሆንም "አፋጣኝ የሆኑ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ከተከሳሾች በጋራ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ስላሉ" ችሎቱ የክስ ማንበቡን ጉዳይ ትቶ የተከሳሾችን አቤቱታ እንዲያደምጥ ጥያቄ ቀርቧል።

አቤቱታውን የተቀበለው ችሎቱ በስፍራው ለዘገባ የታደሙ ጋዜጠኞች እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ተወካይ "ለችሎቱ ፈቃድ አልጠየቃችሁም" በሚል የዛሬውን ችሎት መታደም እንጂ መዘገብ እንደማይችሉ ተነግሯቸው ከችሎቱ ወጥተዋል።

ጠበቆች የተከሳሾችን የመብት ጥሰት አቤቱታ መገናኛ ብዙኃን ሊዘግቡት እንደሚገባ እና እንዲህ ያለ ክልከላ ገጥሞ እንደማያውቅ ጠቅሰው ቢከራከሩም፣ ችሎቱ ከመገናኛ ብዙኃን ዘገባን የተመለከተ ጥያቄ አልቀረበም በሚል ጥያቄ እስካልቀረበ ድረስ ጋዜጠኞች ችሎቱን እንዳይዘግቡ ጥብቅ ትእዛዝ አስተላልፏል።

ይህንን ተከትሎ ወደ ፍርድ ቤቱ አስተዳደር ክፍል በመሄድ ባደረግነው ማጣራት ፣ ችሎት ውስጥ ገብቶ ለመዘገብ የግድ ለእያንዳንዱ ችሎት ማስፈቀድ እንደሚያስፈልግ ተገልጾልን ፣ ሆኖም ለዛሬው ተመልሰን ችሎቱን መዘገብ የምንችልበትን ፈቃድ ባለማግኘታችን ችሎቱን መዘገብ አልቻልንም።ይህ ከሆነ በኋላ የችሎቱ ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ከጠበቆች መካከል አንደኛውን ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝን ጠይቀናቸዋል።

የእስር ቤትን የሚያመለክት ፎቶ (ከክምችታችን)
የእስር ቤትን የሚያመለክት ፎቶ (ከክምችታችን)ምስል picture alliance/dpa/dpa-Zentralbild

 

ተከሳሾች ያቀረቧቸው የመብት ጥያቄዎች 

ተከሳሾቹ  ከሳምንት በፊት እሥር ቤት ውስጥ ሆነው በፃፉት ደብዳቤ "ማንነትን መሠረት ያደረገ ስድብ፣ ዘለፋ ፣ ማስፈራራት፣ ዛቻ ፣ ድብደባ እና ዝርፊያ" እንደተፈፀመባቸው ገልፀው ነበር። በዛሬው ችሎት ላይም አቶ ክርስትያን ታደለ ደረሰብኝ ያሉትን የመብት ጥሰት ለፍርድ ቤቱ መግለጻቸውን ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ በስልክ ነግረውናል።

 

የቀረበው ክስ ጭብጥ

የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዮሃንስ ቧያሌው በሆኑበት በዚህ የክስ መዝገብ ሥር ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስትያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር ካሳ ተሻገር፣ አቶ እስክንድር ነጋ ፣ አቶ ዘመነ ካሴ እና ዶክተር ጫኔ ከበደ ይገኙበታል። 

ለተከሳሾች እና ጠበቆቻቸውየደረሰው የክስ ዝርዝር ተከሳሾች "የፖለቲካ ርዕዮትን በኃይል ለማስፈፀም በማሰብ የአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤትን ዓላማ ለማስፈፀም" ተሰባስበው መምራት የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

 ሰለሞን ዉጬ 

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ